መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 22፤2014-በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ ከ130 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

የትራንስፖርት ቢሮ በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በአግባቡ በመቆጣጠር ነዋሪዎችን ከእንግልትና ተጨማሪ ክፍያ ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ 130 ሺህ 472 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

ህግ በተላለፉ አካላት ላይ በተወሰደ እርምጃም
19 ሚሊዮን 630 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ቅጣቱ የተጣለው ትርፍ በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ከተመደቡበት ርቀት በታች አቆራርጠው በመጫን፣ ታፔላ ባለመስቀል እንዲሁም ተያያዥ ጥፋቶችን በመፈፀማቸው ነው ብለዋል፡፡

ይህም የክትትልና ቁጥጥር ስራው በስፋት እየተሰራ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፥ በቀጣይም የክትትልና ቁጥጥር ስራውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በመዘርጋት አሰራሩን ለማጠናከር እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አረጋዊ በተለይ በበዓላትና በምሽት ወቅት መመሪያን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህግን በተላለፉ ከ96 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል፡፡

ቤተልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *