መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 26፤2014-የሄይቲ ጠቅላይ ሚንስትር ኤሪያል ሄንሪ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተረፉ

ታጣቂዎች የሄይቲውን ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ቅዳሜ እለት በተሰናዳው የሀገሪቱን የነጻነት መታሰቢያ በዓል ላይ ለመግደል መሞከራቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል። ይህው ክስተት ያጋጠመው ሄንሪ በሰሜናዊ የጎናቪስ ከተማ በሚገኝ ቤተክርስትያን በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሳተፉ ነው።

የቪዲዮ ማስረጃዎች እንዳመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አጃቢዎቻቸው በከባድ የተኩስ እሩምታ ወደ መኪናቸው ሲሮጡ ታይተዋል። ባለፈው ሀምሌ ወር የቀድሞ የሄይቲ ፕሬዝዳንት ጆቬኔል ሞይስ በውድቅት ሌሊት በተኙበት በ12 ጥይት ተደብድበው ከተገደሉ በኋላ የጸጥታው ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ከግድያው ሙከራ ጀርባ “ሽፍቶች እና አሸባሪዎች” እንዳሉበት የገለጸ ሲሆን በተጠርጣሪዎቹ ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱን አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ጥቃት ፈፃሚው ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ልዑክ ለማጥቃት የነበሩበት በቤተክርስቲያን መክበቡን ይፋ አድርጓል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በታጣቂዎቹ እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ አንድ ሰው ሲገደል 2 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሚኪያስ ፀጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *