መደበኛ ያልሆነ

ጥር 3፤2014-በአፋር ክልል 90 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች መማር የማስተማር ሂደት ተጀምሯል

በአፋር ክልል የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ባደረሰው ጥቃት እና ውድመት የተነሳ ተቋርጦ የነበርው ትምህርት 90 በመቶ የሚሆኑ ቦታዎች ላይ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አህመድ ያዬ ከብስራት ሬድዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በሽብርተኛው ቡድን የወደሙ የትምህርት ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሰሩ የርብርብ ስራዎች 90 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት እንዲጀምር መደረጉን አንሰተዋል፡ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበር ያነሱት አቶ አህመድ በያዝነው ሳምንት በመደበኛ ትምህርት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተወሰነ መልኩ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ያላኩ መኖራቸውንም አቶ አህመድ የጠቆሙ ሲሆን ለዚህም ምክንያት ደግሞ አካባቢውን ለቀው የወጡ ሰዎች እንዳሉ አንስተዋል፡፡

የመምህራን እና የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ያሉባቸውን ቦታዎች በመለየት ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሙሉ በሙሉ ትምህርት ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።ተማሪዎች በጦርነት ውስጥ ነን የሚል ሀሳብም እንዳይኖራቸው በአስቸካይ ወደትምህርት ገበታቸው መመለስ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አህመድ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል 4 ዞኖችና 21 ወረዳዎች ባደረሰው ጉዳት 694 ትምህርት ቤቶች በከፊል፣ 65 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በድምሩ 759 ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ይታወሳል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *