የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ላይ የተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን በሚኒስትሩ የተነሱ ዋና ዋና ሀሳቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
- ጀግኖች ሰማዕታትን የመዘከር፣ ዕውቅና እና ሽልማት መስጠትን በተመለከተ፤
• የኢትዮጵያን ኅልውና በመታደግ ውድ ህይወታቸው ለገበሩ፣ ከፍተኛ አበርክቶ ለነበራቸው የምንጊዜም ጀግኖችን የመዘከር፣ ዕውቅና እና ሽልማት ከመስጠት በኩል፤ መንግሥት ከወታደራዊ ማዕረጎች እና ኒሽኖች በተጨማሪ ለአገራቸው ውድ ዋጋ ለከፈሉ እና ጉልህ አበርክቶ ላሳዩ ጀግኖች ብቻ የሚሰጠውን የጥቁር አንበሳ እና የዓድዋ የመጨረሻ ከፍተኛ ሜዳይ እንዲሸለሙ አድርጓል።
• በተጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም የመከላከያ ሠራዊታችን እጅግ በርካታ ተግባራት ቢፈፅምም ካለንበት ጂኦፓለቲካዊ እና ውስብስብ የፀጥታ እንዲሁም የተለያዩ ስጋቶች አኳያ ራሱን የማዘመን፤ የማደራጀት እና ልቆ ለመገኘት የሚያበቃውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እየተሰነዘሩብን ያሉ ጥቃቶችም ገና እልባት ያላገኙ በመሆኑ ታሪካችንን፣ የሕዝቦቻችንን ፍላጎት እና የምንመኘውን አይነት ኅብረብ-ሔራዊ እና ሉዓላዊ አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል ግንባታ ማካሄድ ይጠበቅበታል።
• ሕዝባችንም ይህን ተገንዝቦ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤
- የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጥን በተመለከተ
• ከፖለቲካ ልሂቃን አልፈው ወደ ማኅበረሰቡ እየተንጸባረቁ ያሉ ያለመግባባት ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ከስር መሠረቱ ለመፍታት በመደበኛ ፍትህ ብቻ ሳይሆን በተሃድሶ የሽግግር ማዕቀፍ ጭምር እልባት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት ያምናል።
• መንግሥት እንደ አንድ ተዋናይ ለአካታች ምክክር መድረኩ የተመቻቸ ፖለቲካዊ ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅበታል፤ ለስኬታማነት መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ መክፈልም ይገባል።
• ዘላቂውን ሕዝባዊ እና አገራዊ ጥቅሞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለሀገራዊ ምክክሩም አካታችነት እና ስኬት ሲባል በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ሕጋዊ እና ተቋማዊ አሠራርን በጠበቀ አኳኋን መፍታት ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ የተወሰኑ እስረኞች ክስ ተቋርጧል።
• የክስ መቋረጥ ውሳኔ ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ያለመ ነው።
o የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ከእልህና ከመጠፋፋት ፖለቲካ በራቀ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ሊያረጋግጥ በሚችለው በአገራዊ አካታች ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለመፍታት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፤
o ሁለተኛው ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት እና ሉዓላዊ አንድነትን ከአደጋ ለመታደግ ተብሎ የተወሰደ ፖለቲካዊ እርምጃ ነው።
2.1. የውሳኔው ድንገተኛነት እና ከውሳኔው በኋላ የታዩ አዝማሚያዎች
• የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ነው።
ይህ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሕዝብ ውክልና ያለው፤ ሕግ እና ሥርዓትን ተከትሎ የሚሠራ በምልአተ ሕዝቡ ጥቅሞች፣ በኅብረ-ብሔራዊ፣ ሉዓላዊ አንድነትና በሕግ የበላይነት የማይደራደር መንግሥት ነው።
• መንግሥት ካለፉት ልምዶች በመነሳት ጠንካራ ተቋማት እየገነባ ነው። ተቋማቱም ነፃ ሆነው ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ።
• ካለፉት ቁርሾዎቻችን እና ካሳለፍናቸው መከራዎች አኳያ በመንግሥት ሰሞነኛ ውሳኔ ላይ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው ተገቢ አይደለም ባይባልም ከራሱ ከመንግሥት ባህሪ ሕዝባችን እምነቱን ማሳደር አለበት።
• መንግሥት ጠንካራ ነፃ ተቋማትን እየገነባ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ትክክለኛ የመንግሥት ባህሪን መላበስ አለበት። ባለው ማኅበራዊ ኮንትራት የሕዝብ እና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን ያለ ምንም ጫና መወሰንና መተግበር አለበት። ለውሳኔዎቹም ሙሉ ሃላፊነት መውሰድ አለበት። ይህ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት መርህ ነው።
• በቀጠይ ለአካታች ብሔራዊ ውይይቶቹ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላም ለማስፋን በሚወሰዱ የፖለቲካ እርምጃዎች ዙሪያ አመራሩ ጊዜ ወስዶ እንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም በመሠረታዊ መርሆዎቹ እና አቅጣጫዎቻቸው ላይ ሰፋፊ ውይይቶችን አድርጓል።
ለአገራዊ አካታች ምክክሩ ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የተወሰኑ እስረኞች ክስ መቋረጥ እንደሚገባም በአመራሩ መካከል ስምምነት አለ።
ከዚህ አኳያ በተወሰነ አካል ብቻ የተወሰነ ውሳኔ ተደርጎ የሚወራው ወሬም መሠረተ ቢስ ነው።
2.2 ክሱ ሲቋረጥ እነዚህ ግለሰቦች ግጭት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ፤
• የመጀመሪያው ጉዳይ መንግሥት ክስ አቋረጠ እንጂ ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ ናቸው አልተባለም፤ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ወገኖችም ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው የተሻለ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲችሉ ዕድል የተሰጣቸው ስለሆነ ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን ይክሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
• መንግሥት ያለፉ ዋጋ እስከፋይ እና ግጭት ጠማቂ አካሄዶችን በጭራሽ እንዲደገሙ አይፈቅድም፤ በእነዚህ ጉዳዮች መንግሥት ድርድር የለውም።
• ውሳኔው ያገኘነውን ድል የሚያደበዝዝ ሳይሆን ለዘላቂ ድል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
የውሳኔውን መነሻና ፋይዳ በሰከነ መልኩ ስንፈትሽ ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም መረጋገጥ የሚያግዝ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚቀንስ፤ በአውደ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክ እንድንደግም የሚያደርግ፤ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት