በ2014 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ከ539 ሚሊየን 583 ሺ ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የተሰበሰበው ገንዘብ ከሀገር ውስጥ እና በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሲሆን ገንዘቡ የተገኘው ከቦንድ ግዢ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች መሆኑን የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ አብርሀም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።
ከ204 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከዲያስፖራው የተገኘ ሲሆን 216 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ እና ልገሳ ተሰብስቧል። በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ብቻ የተሰበሰበው ገቢ 44 ሚሊየን ያህል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡የግድቡ ግንባት ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ፣ ከውጪ እና ከቦንድ ሽያጭ ልገሳ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች ከ16 ቢሊዮን 268 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስባል፡፡
አሁን ላይ መላው ኢትዮጵውያን የህልውና ዘመቻ ላይ ቢሆንም እንኳን ለግድቡ የሚደረጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠሉ ተጠቁሟል፡፡በቅርቡ የታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብ በሁለቱ ተርባይነር የኤሌክትሪክ ሀይል እንሚያመነጭ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መግለፁ ይታወሳል፡፡
በትግስት ላቀዉ