የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ አደባባዮችን ፣መንገዶችን እና ታቦት ማደሪያ ስፍራዎችን ለማሳመር ተብለው የሚሰሩ ስራዎች ለአደጋ ስጋት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ እና በባለሙያ መታገዝ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ከብስራት ሬድዮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደተናገሩት ከሶስት ዓመት በፊት አዲሱ ገበያ አካባቢ አራት ወጣቶች ታቦታቱ የሚሄዱበትን ሰረገላ ሲገፉ ፤ሰረገላው ከረገበ ኤሌክትሪክ ጋር ተገናኝቶ የወጣቶቹ ህይወት ማለፉን ያስታወሱ ሲሆን አሁንም በከተማዋ ላይ እየተሰሩ ያሉ የጥምቀት በዓል ስራዎች አደጋን ታሳቢ ተደርገው በጥንቃቄ እና ባለሙያ በታከለበት መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ንጋቱ ማብራሪያም ጊዜያዊ ኤሌክትሪክ በሚዘረጋባቸው የታቦታ ማደሪያ ድንካኖች እና መድረኮች ሲዘጋጁ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ አብራርተዋል፡፡የኤሌክትሪክ ገመዶች ከሰው ቁመት በላይ ማድረግ ፣ አንጸባራቂ ምልክቶች እና ኤሌክትሪክ የሚዘረጋባቸው እንጨቶችም በጥልቅ በተቆፈረ ጉድጋድ መቀበር እንዳለባቸው እንስተዋል፡፡
ታቦታ በሚያልፉበት መንደሮች የታቦታት ማጀቢያ ሰረገላዎች ከረገቡ ኤሌክትሪኮች መስመሮችም ጋር እንዳይገናኙ ማረጋገጥ የረገቡም ካሉ አስቀድመው ለኤሌክትሪክ ሀይል ማሳወቅ እና መሰራት እንዳለባቸው አቶ ንጋቱ አስረድተዋል፡፡በበዓሉ እለትም የጸበል አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዳይለይ ኮሚሽኑ ያሳሰበ ሲሆን የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ከቤተክርስቲያናት ጋር በመነጋገር ታቦታት ማደሪያ ቦታዎች ላይ አብረው የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየሠሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
በትግስት ላቀው