መደበኛ ያልሆነ

ጥር 12፤2014-በፀጥታ ስጋት የተነሳ በቡርኪናፋሶ ፌስቡክ ተዘጋ

በቡርኪናፋሶ መንግስት በጸጥታ ስጋት የተነሳ የፌስቡክ አገልግሎት እንዲቋረጥ ካደረገ ከሳምንት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የቡርኪናፋሶ የመንግስት ቃል አቀባይ አልካሶም ማይጋ ከ10 ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የፌስቡክ አገልግሎት መዘጋቱን በተመለከተ ማብራሪያ እንዳልተሰጣቸዉ ገልጸዉ የነበረ ቢሆንም አሁንም አገልግሎቱ አልተመለሰም፡፡

እኔ እንደማስበው ያለዉ የጸጥታ ችግር እንዲስፋፋ ካለመፍቀድ እና ባለዉ ሁኔታ ላይ አነስተኛ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ በመሆኑ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅም መቅደም እንዳለበት ግልጽ በመሆኑ ፌስቡክ እንዲዘጋ ሆኗል ሲሉ ቃል አቀባዩ ማይጋ ከታዋቂዉ የቡርኪናፋሶ ሬዲዮ ጣቢያ ኦሜጋ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል፡፡

የቡርኪናፋሶ መንግስት ከቀናቶች በፊት ስምንት ወታደሮች የመንግስት ተቋማትን የማተራመስ እቅድ ነበራቸዉ በሚል በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን መንግስትን በሀይል የመገልበጥ ሴራ እንደነበር ገልጿል፡፡የኢንተርኔት ነፃነት ተቆጣጣሪ ቡድን ኔትብሎክስ በቡርኪናፋሶ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እንዳለ ይፋ አድርጓል።

ባለፈው ህዳር ወር በሽብርተኛ ቡድን አባላት በደረሰ ጥቃት 53 ሰዎች መገደላቸው በመንግስት ላይ ያለዉ ተቃውሞ እንዲበረታ በማድረግ ህዝባዊ ቁጣውን ከፍ አድርጎታል። አመፁ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋትን ጨምሯል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *