መደበኛ ያልሆነ

ጥር 16፤2014-ህወሃት በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን ጦርነት ከፍቷል ሲል የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል በአብአላና በመጋሌ ወረዳ የከፈተውን ውጊያ አጠናክሮ መቀጠሉን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ። ቡድኑ ምንም አይነት ሰብአዊነትና ርህራሄ ፈፅሞ ሳያሳይ በንፁሀን ዜጎች ላይ ከባድ መሳሪያ በመክፈት እያሸበረ ይገኛል ሲል የክልሉ መንግስት ገልጿል፡፡

እያደረሰ ባለው ጥቃትም የአፋር ንፁሃን ኢላማ በማድረግ የሽብር ተግባሩን በማስፋት ላይ መሆኑንም ገልጿል። በዛሬው እለትም በኪልበቲ ረሱ ዞን በተለያዩ ቦታዎች የአፋር ክልልን ወሰን ጥሶ በመግባት በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንፁሀንን ለጉዳት መዳረጉንም አስታውቋል።

ይሁንና ሁሌም በማጭበርበርና በውሸት ፕሮፖጋንዳ እድሜውን የሚያራዝመው ቡድኑ በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ዘልቆ በመግባት ንፁሀን የጎዳ ቢሆንም ጥቃት እንደተፈፀመበት አስመስሎ በማቅረብ አሁንም ማደናገሪያውን እየነዛ ይገኛል። ሲልም ነው የክልሉ መንግስት ያስታወቀው።የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ “የህወሃት ቡድን በአራት ዞኖች ውስጥ በ 21 ወረዳዎች ወረራ በማካሄድ የአፋር ህዝብን በአሰቃቂ ሁኔታ ቢጨፈጭፍም፣ በብዙ ቢሊየኖች የሚገመት ሀብት ንብረት ቢያወድም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ እንዲሰደድ ቢያደርግም ለጎረቤት ትግራይ ህዝብ ሰብአዊነት ሲባል እርዳታ በአፋር አብአላ በኩል እንዲያልፍ እየተደረገ ነበር።” ብሏል።

“በአፋር በተለያዩ አካባቢዎች ወረራ አካሂዶ በሁሉም ግንባሮች ሽንፈትን አስተናግዶ የወጣው ቡድኑ፣ አሁንም እንደ አዲስ በኪልበቲ ረሱ (ዞን) በኩል በከፈታቸው ግንባሮች የምድር ድሮኖቹ አስፈላጊውን መከታና ማጥቃት በማካሄድ የቡድኑን እብደት የሚያመክን በመሆኑ፣ ቡድኑ ዘልቆ ገብቶ ለመውረር ያስገባውን ሀይሉን አስቀድሞ ሊያወጣ ይገባል” ሲልም የክልሉ መንግስት አሳስቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *