
በሜዲትራኒያን ባህር አካባቢ በደረሰ ከባድ የበረዶ አውሎ ንፋስ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎች በግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ዙሪያ ባለው አውራ ጎዳና ላይ ታግተው ቆይተዋል፡፡ አሽከርካሪዎች ለአንድ ሌሊት በሙሉ ታግተዉ ከቆዩ በኃላ ከሞት መትረፋቸዉ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ባለፉት 24 ሰዓት ከ3,500 በላይ አሽከርካሪዎች ከበረዶዉ ግግር እንዲወጡ የተደረገ ቢሆንም 300 የሚጠጉ አሽከርካሪዎች አሁንም አቲኪ ኦዶስ በተሰኘዉ አውራ ጎዳና ላይ እንዲቆዩ አስገድዷል፡፡የአቴንስ አንዳንድ ክፍሎች በከባድ የሃይል መቆራረጥ የተመቱ ሲሆን የሀይል አቅርቦቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየሰሩ ይገኛል ተብሏል፡፡
የግሪክ ጎረቤት የሆነችዉ ቱርክ በአስከፊ የአየር ሁኔታ ዉስጥ የምትገኝ ሲሆን እስከ 31 ኢንች በረዶ መዉረዱም ተጠቁሟል፡፡ከዓለማችን ትልቁ የሆነው የኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ የአዉሮፕላን ማኮብኮቢያዎች በበረዶ የተሸፈነ ሲሆን የአንዱ የካርጎ ተርሚናል ጣሪያ በከባድ በረዶ መደርመሱን ተከትሎ ሰኞ እለት ተዘግቶ ዉሏል፡፡
በሚኪያስ ፀጋዬ