
እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የአፓርታይድ ወንጀል በመፈጸም የበታች ቡድን አድርጋ በመመልከቷ ተጠያቂ መሆን አለባት ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታዉቋል፡፡በትላንትናዉ እለት የተለቀቀው ባለ 280 ገጽ ሪፖርት ላይ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ የእስራኤል ባለስልጣናት በፍልስጤማውያን ላይ የጭቆና እና የአገዛዝ ስርዓትን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ በዝርዝር ያሳያል፡፡
በምርመራዉ እንደተረጋገጠዉ የፍልስጤም መሬት እና ንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ፣ ህገወጥ ግድያ፣ የግዳጅ ዝውውር፣ ከባድ የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ አስተዳደራዊ እስራት እና ዜግነት ለፍልስጤማውያን መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች በእስራኤል እንደሚፈጸሙ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል።በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ድርጊቱ የአፓርታይድ ስርአት አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ተለዋጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ሪፖርቱን “ከእውነታው የራቀ ” በማለት ያጣጣሉ ሲሆን “አምነስቲ በአሸባሪ ድርጅቶች የሚጋሩትን ውሸቶች ያስተጋባል” ሲሉ ከሰዋል።አምነስቲ ጸረ ፂኆናዉን አጀንዳ አለዉ ሲሉ ከሰዋል።
የዩሮ-ሜድ የሰብዓዊት መብት ቡድን ሊቀመንበር ራሚ አብዱ እንደተናገሩት እስራኤል ለበርካታ ዓመታት የምትፈጽመዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ “ፀረ ፂኆናዉን” በማለት ታሸማቅቃለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሚኪያስ ፀጋዬ