በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች የአካል ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚካሄደው የአባል አገራቱ 40ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው ዕለት መጀመሩ ይታወሳል።የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉባኤውን ለመታደም ለተገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዲኘሎማቲክ ማህበረብ አባላት በትናንትናው ዕለት ምሽቱን የእራት ግብዣ አድርገዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው ብለዋል።አክለውም የተቀናጀውን የአንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና አገራት ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በአፍሪካውያን ወንድማዊ ድጋፍ ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተጠርቶ የነበረው የጄኔቫው ጉባኤ የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ ልዩ ጉባኤው የአንድም አፍሪካ አገርን ድጋፍ እንዳላገኘ በንግግራቸው በመግለፅ የአፍሪካውያን ምን ያህል ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆሙ አሳይተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በድምፃቸው መንግስታቸውን መምረጣቸውን አስታውሰው፣ ተመራጩ መንግስት ከቀደሙት በተለየ በካቢኔው ውስጥ ተቃዋሚዎችን ማቀፉን ጠቅሰዋል።በቅርቡ በእስር ላይ የሚገኙ የፓለቲካ ሰዎችን መፍታቷን አንስተዋል።
በተግዳሮቶችም ውስጥ ሆና ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ እየጣረች እንደምትገኝ ያመለከቱ ሲሆን፤ ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብን እንደ አንድ ማሳያ ነዉ ማለታቸዉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።