
የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ2014 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከስምንት ሎተሪዎች ለሽያጭ እና የእድል ጨዋታ በማቅረብ 550.2 ሚሊየን ብር ጠቅላላ ገቢ ማግኘቱን አስታዉቋል፡፡ገቢዉ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ14.8 ሚሊየን ብር ብላጫ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡አስተዳደሩ ለሽያጭ እና ለእድል ጨዋታ ኮሚሽን ካቀረባቸው ሎተሪዎች ውስጥ 144.8 ሚሊየን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በአንዳንድ አካባባዎች በነበረ የፀጥታ ችግር የተነሳ ዘጠኝ የሚሆኑ የአስተዳደሩ ቢሮዎች ዝግ በመሆናቸዉ በቂ ሎተሪ ለገበያ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም የሎተሪ ህትመት ችግር በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ባለመኖሩ እና ህትመት መዘግየቱ ከነበሩ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደደር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴድሮስ ንዋይ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡
ፍቃድ ያልተሰጣቸው ህገ ወጥ የእድል ጨዋታዎች በአስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ችግር በመፍጠራቸዉ ህገወጥ ጨዋታ በሚያካሄዱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ይህንኑ ተከትሎ 120 ግለሰቦች ላይ ክስ ሲመሰረት 16 በሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ደግሞ የ3 ዓመት እስር እና የ50 ሺ ብር ቅጣት መተላለፉም ተገልጿል፡፡
የቅጣት እርምጃ ከተላለፈባቸዉ ውስጥ በአዲስ አበባ ፣አዳማ እና ሞጆ አካባቢዎች ላይ ያሉት ከፍተኛ ቁጥር አላቸዉ፡፡ባለፉት ስድስት ወራት ከማስተዛዘኛ እስከ 20 ሚሊየን ብር ለባለእድለኞች 219 ሚሊየን ብር ተሰጥቷል፡፡10ሺ ለሚሆኑ ሎተሪ አዞሪዎች እና ሎተሪ ለሚያከፋፍሉ ወኪሎች 80 ሚሊየን ብር በኮሚሽን መልክ መክፈሉን አቶ ቴድሮስ ንዋይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ሳምራዊት ስዩም