መደበኛ ያልሆነ

የካቲት 7፤2014-አሜሪካ በቀጣዮቹ 48 ሰዓታት ከዩክሬን የኤምባሲ ሰራተኞቿን ልታስወጣ መሆኑ ተሰማ

ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ሁሉንም ሰራተኞቿን ከኪየቭ ለማስወጣት በዝግጅት ላይ መሆኗን ሶስት ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡እንዲህ ዓይነቱን የፍርሃት ዉሳኔ የተቹት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ፣ ሩሲያ በሚቀጥሉት ቀናት ወረራ ለማድረግ እንዳቀደች ምንም አይነት ማረጋገጫ እንዳላዩ ተናግረዋል።

ዩክሬን በድንበርዋ አካባቢ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ከሩሲያ እና ቁልፍ የአውሮጳ ህብረት የጸጥታ ቡድን አባላት ጋር ዉይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች፡፡የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያ የወታደሮቿን አደረጃጀት በተመለከተ እንድታስረዳን ያቀረብነዉን መደበኛ ጥያቄዎችን ችላ ብላለች ሲሉ ተናግረዋል።

ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነዉ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ሩሲያ እቅዷን በግልጽነት እንድታስረዳ ዩክሬን ስብሰባ መጥራቷን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡በዩክሬን ድንበር ላይ ወደ 100,000 የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች ቢገኙም ሞስኮ ዩክሬንን የመውረር እቅድ የለኝም ስትል በተደጋጋሚ ታስተባብላለች፡፡

ነገር ግን አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ሞስኮ በአየር ላይ ቦምብ በመወርወር በማንኛውም ጊዜ ዉጊያ ልትጀምር ትችላለች ስትል አስጠንቅቃለች። ከ12 በላይ ሀገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰቡ ሲሆን የተወሰኑት የኤምባሲ ሰራተኞቻቸዉን ከዋና ከተማው እንዲወጡ አድርገዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *