በቦሌ ክፍለከተማ ከሚገኙ 11 ወረዳዎች ዉስጥ በሶስት ወረዳዎች ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው ድንገተኛ ከ 717 በላይ የሺሻ ማስጨሻ እቃዎች እንደተያዙ የቦሌ ክፍለ ከተማ ምግብ ፣ መድኃኒት ፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ፋንታነሽ ሰለሞን በተለይ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።
በክፍለከተማዉ በተደረገዉ ቁጥጥር በኢትዮጵያ መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ ያልተሰጣቸው በህገወጥ መንገድ የገቡ መድኃኒቶች ፣ የህጻናት ምግቦች እና የታቸገ ወተት ፣ የለስላሳ እና የጁስ መጠጦች ተይዘዋል፡፡በተጨማሪም ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ፣ ከአምራች አካል የተቀመጡ የምርት መግለጫ የሌላቸዉ ምርቶች ፣ የዉበት መጠበቂያዎች ፣ ጊዜያቸዉ ያለፈባቸው የሴቶች እና የህጻናት የንጽህና መጠበቂያዎች ጨምሮ የሲጋራ እና የሺሻ ማጨሻ እቃዎች ሊያዙ ችለዋል፡፡
ክፍለከተማዉ ባደረገዉ ቁጥጥር የተያዙ ህገወጥ እቃዎችን ለሁለት ቀናት ለህዝብ ክፍት አድርጎ አሳይቷል። በቁጥጥሩ የተያዙትን ምርቶቹ ለተጠቃሚ ለማስተላለፍ ሲሞክሩ የነበሩ ተቋማት እና ግለሰቦችም ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ወ/ሮ ፋንታነሽ ሰለሞን አክለዉ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል ።
በበረከት ሞገስ