
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ስላለው ቀውስ ለመወያየት በመርህ ደረጃ መስማማታቸዉ ይፋ ተደርጓል፡፡ፈረንሳይ ያቀረበችው ውይይት የሚካሄደው ሩሲያ ጎረቤቷን ዩክሬንን ካልወረረች ብቻ ነው ሲሉ ዋይት ሀውስ አስታውቋል።
ውይይቱ ባለፉት አሥርተ ዓመታት በአውሮፓ ውስጥ ከታዩት አስከፊ የጸጥታ ቀውሶች አንዱ የሆነውን የዩክሬን ዉጥረት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል፡፡የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት የስለላ መረጃ ሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ያሳያል ቢሉም ሞስኮ ግን የሀሰት ስትል ታስተባብላለች፡፡
የዉይይት ሀሳቡ ሊመጣ የቻለዉ በፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና በሩሲያ አቻቸዉ ፑቲን መካከል ሁለት የስልክ ጥሪ ከተደረገ እና በአጠቃላይ ሶስት ሰዓታት ከፈጀ ንግግር በኃላ ነዉ፡፡የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሐሙስ ዕለት በሚያደርጉት ውይይት ስለየመሪዎች ጉባኤ ዝርዝር ጉዳይ እንደሚወያዩበት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ባወጣዉ መግለጫ አስታዉቋል፡፡
በስምኦን ደረጄ