መደበኛ ያልሆነ

ጥር 15፤2015-አዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ከአራት ፖርኮቿ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የመናፈሻ አገልግሎትን በማሻሻል 6.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ4.9 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታውቋል።የቢሮው ምክትል ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት የተገኘው አፈጻጸም በመቶኛ ሲሰላ 76 በመቶ መሆኑ ገልጸዋል።

ይህ ገቢ የተገኘውም ከአፍሪካ፣ብሄረ ጽጌ፣ አምባሳደር እና ከንቲባ ቢትወደድ ወልደጻዲቅ ጎሹ ፓርኮች እንደሆነ ተገልጿል።በዘንድሮው ግማሽ ዓመት የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በገቢም ሆነ በጎብኚዎች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡ ባለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከ4.1 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ2ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ምክትል ቢሮ ሃላፊዋ ይመኙሻል ገልጸዋል።

በጎብኚዎች ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ፓርኮቹን መጎብኘታቸዉን ገልጸዋል፡፡በዘንድሮ በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም የተገኘው ከዚህ ቀደም ተዘግተው የነበሩ መናፈሻዎች ጥገና ተደርጓላቸው ዳግም ስራ በመግባታቸዉ የተነሳ ነዉ፡፡በሌላ በኩል ባለፈው አመት የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የነበሩ ትልልቅ መሰናዶዎችን ለገቢዉ መጨመር አስተዋጾ አድርጓል፡፡

በቀጣይ የተሻለ ገቢን ከእነዚሁ ፓርኮች ለማግኘት ጥረቶች ይደረጋሉ ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ የህጻናት መጫወቻ የሌላቸው ፓርኮች አገልግሎታቸው የተሟላ ለማድረግ እንደሚሰራ ጨምረዉ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *