መደበኛ ያልሆነ

ጥር 17፤2015-የጋምቤላ ክልል የመንግስትን በጀትን አለአግባብ በማዉጣት ለራሳቸዉ ካደረጉ የወረዳ ባለስልጣናት 15 ሚሊዮን ብር ተመላሽ ማድረጉን አስታወቀ

የጋምቤላ ክልል ፋይናንስ ቢሮ በባለፈዉ አመት የኦዲት ግኝት የመንግስት በጀትን አለአግባብ እንዲወጣ እና ለራሳቸዉ ጥቅም እንዲዉል ካደረጉ የወረዳ አመራሮች 15 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን የቢሮዉ ኃላፊ አቶ ኡባንግ ኦቶዉ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።እንደ ቢሮዉ ኃላፊዉ ገለጻ ፤ የተጠቀሰዉ ገንዘብ ተከፋይ በሚደረጉ በተለያዩ አበሎች ላይ ሂሳብ ሳያወራርዱ የቀሩ እና አለአግባብ ወጪ ያደረጉትን ገንዘብ ተመላሽ ካላደረጉ ወረዳዎች መገኘቱንም ተናግረዋል።

ቢሮዉ በኦዲት ግኝቱ ወቅት የሚኖሩ ዉጤቶችን መሰረት በማድረግ ወረዳዎች ወይንም የወረዳ አመራሮች የጎደለዉን ገንዘብ በቀነገደብ ተመላሽ እንዲያደርጉ ያሳሳባል ብለዋል።ሆኖም የተቀመጠላቸዉን ቀነ ገደብ በማያከብሩና ገንዘብ በማይመልሱ ግለሰቦች ላይ በወንጀል ጭምር እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል። ነገርግን ይህ እስካሁን ተግባራዊ እንዳልተደረገም አክለዋል።

በክልሉ ለሚስተዋለዉ በጀትን አለአግባብ ወጪ ማድረግና ጉድለት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት ለወረዳ አመራሮች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ለሚጎድልና ከሂሳብ ለሚጠፋ ገንዘብም አመራሮቹ ሀላፊነት እንደሚወስዱ በርዕሰ መስተዳድሩ ተነግሯቸዋል ተብሏል።በባለፈዉ አመትም በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች በጀትን ያላገናዘበ ቅጥር በመፈጸም ለሚያጋጥማቸዉ የበጀት እጥረት ፤ ከ 1 መቶ 61 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከክልሉ መንግስት መበደራቸውን ብስራት ራዲዮ መዘገቡ ይታወሳል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *