መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 18፤2015-ሩሲያ ዩክሬንን እንደማታሸንፋት አሜሪካ ተናገረች

ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ ድል እንደማታገኝ አሜሪካ ያስታወቀች ሲሆን የዩክሬን ሃይሎች ቢሆኑ በቅርቡ የሩሲያ ወታደሮችን ከግዛቶቻቸዉ ጠራርገዉ የማስወጣት ዕድል የላቸውም ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ተናግረዋል። ይህንን ጦርነት፣ በወታደራዊ ረገድ ከሄድን ሩሲያን አሸናፊ አያደርጋትም ሲሉ የተደመጡት የዩናይትድ ስቴትስ የጋራ የጦር አለቆች ሊቀመንበሩ ጄኔራል ማርክ ሚሌይ ናቸዉ፡፡

የዩክሬንን መንግስት መጣልን ጨምሮ የሩሲያ ዋና ስትራቴጂካዊ ዓላማዎች “በወታደራዊ መንገድ ሊሳኩ የማይችሉ ናቸው” ሲሉ አክለዋል። ሚሌይ ይህንን የተናገሩር የዩክሬን መከላከያ ግንኙነት ቡድን አባላት ከሆኑ በርካታ ሀገራት ጋር ስብሰባ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። ይህዉ ለዩክሬን ድጋፍ የሚሰጠዉ ቡድን ራምስታይን በመባል ይታወቃል።

በሌላ በኩል በዩክሬን ውስጥ አሁንም  በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሩስያ ወታደሮች አሉ ይህ ደግሞ በሞስኮ ኃይሎች የተያዘውን ግዛት ዩክሬን መልሳ ለመያዝ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ”የሚሳካ አይመስልም ብለዋል፡፡እንዲያም ሆኖ ግን ውጊያው ይቀጥላል፣ ደም አፋሳሽነቱ ይጨምራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካን አስተያየት የሞስኮ ሰዎችም ከጦርነቱ መቀጠል ጋር በተያያዘ እንደተጋሩት አልጃዚራ ዘግቧል።ለዚህም ማሳያው የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር የሆኑት እና የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በዩክሬን ውስጥ ሩሲያ የገባችበት ጦርነት ለአስርተ ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።ሐሙስ ዕለት በሩሲያ የዜና ወኪል በኩል በቀረበ ዘገባ መሰረት ሜድቬዴቭ ከዩክሬን ጋር ከዓመታት በፊት በ2014 ዓመት ሲደረግ የቆየው ጦርነት፣ እንደገና መጀመሩ ለጦርነቱ መራዘም አመላካች ነው ባይ ናቸው።

የሩሲያ የዜና ወኪል ሜድቬዴቭ በቬትናም ባደረጉት ጉብኝት “ይህ ግጭት በጣም ረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል” ሲሉ መናገራቸውን ዘግቧል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *