መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 6፤2015-“ልጅቷን ቢሠጡኝ ባለኝ አቅም ከልጆቼ ጋር አብሬ ማሳደግ እፈልጋለሁ” ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ሽቤ

ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ሽቤ በባህርዳር ከተማ 6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የትራፊክ ፖሊስ ሲሆኑ ፤ ሰኔ 5/2015 በሥራ ቦታቸዉ ተጥላ የተገኘች የ5 ቀን እድሜ ያላት ሕጻን በርሃብ ስታለቅስ የእናትነት አንጀታቸው አልችል ስላላቸው ጡት በማጥባት የሕጻኗን ርሃብ አስታግሰው ከሞት ታድገዋል፡፡

የ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሕጻኗን ጤንነት በሕክምና ካረጋገጠ በሗላ ለሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት አስረክቧል፡፡

ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ የአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ጡት የሚያጠቧት ሕጻን ልጅ አላቸዉ።

ሕጻኗን ጡት አጥብተው ሕይወቷን ማትረፍ በመቻላቸው መደሰታቸውን በመግለጽ ፤ ሕጻኗን ባላቸው ደመወዝ ከወለዷቸዉ ልጆች ጋር በጋራ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸውና ሕጻኗ እንድትሰጣቸው መጠየቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሸን አስታውቋል፡፡

የ6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ በበኩላቸዉ፤ ዋና ሳጅን ሙሉጎጃም ያጠቧትን ሕጻን እንዲያሳድጓት ለመስጠት ከሴቶችና ሕጻናት መምሪያ ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ምትኩ የተባሉ በድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ፖሊስ መሬት በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ የሆኑ መኮንን ፤ ከተወለደ አንድ ወር የሆነውን እና በድሬዳዋ ከተማ 09 ቀበሌ ገራዳ በሚባል አካባቢ ባለ ድልድይ ሥር ተጥሎ የተገኘውን ልጅ ጡታቸውን በማጥባት ሕይወቱን መታደጋቸው ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *