በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 08 ግደይ ህንጻ ጀርባ ያሉ ከ 80 በላይ አባወራዎች በአንድ ግለሰብ ግንባታ ምክኒያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸዉ ቅሬታቸዉን ለብስራት ራዲዮ ያቀረቡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከ 10 ቀናት በላይ አገልግሎቱ ተቋርጦብናል የሚሉት ነዋሪዎቹ ቁጥራቸዉ ከ 80 እስከ 100 የሚጠጉ አባወራዎች ሲሆኑ በተደጋጋሚ ብልሽት በሚጋጥመዉ አካባቢ ጥገና ቢደረግም ችግሩ በቋሚነት ሊቀረፍ አልቻለም ብለዋል።
የአዲስአበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቂርቆስ ክ/ከተማ ዲስትሪክት የቡድን መሪ የሆኑት አቶ መስፍን ብርሃኑ አካባቢዉ ላይ እየተከናወነ ባለዉ ግንባታ ምክንያት ለመንደሩ ኃይል የሚያቀርበዉ መስመር ላይ በተደጋጋሚ እንጨት እና ሌሎች ቁሳቁዎች እየወደቁ እንደሚበጠስ እንዲሁም የግንባታዉ አጥር ትራንፎርመሩን እጅጉን ተጠግቶ በመሰራቱ ችግር እየፈጠረባቸዉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ ግንባታዉን በሚመለከት ለወረዳዉ በተደጋጋሚ ሪፖርት ማድረጋቸዉን ፤ አጥሩም እንዲፈርስ ምክረ ሀሳብ መስጠታቸዉን ገልጸዋል። በተደጋጋሚ በሚያጋጥመዉ ብልሽት ምክኒያትም አገልግሎቱ ለጥገና በሚል ለወጪ መዳረጉን አመላክተዋል።
ሆኖም ከወረዳዉ ምላሽ ባለመገኘቱ አሁንም ከ80 በላይ የሚጠጉ አባወራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥባቸው ሆኗል። ብስራት ራዲዮ የቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 08 ምላሽን ይዞ የሚመለስ ይሆናል።
በበረከት ሞገስ