
በሲዳማ ክልል ሐዋሳ እና በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተሞች፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ኢንስፔክሽን ቡድን አደረኩት ባለዉ የመስክ ምልከታ የአሰራር ክፍተት በተገኘባቸው አምስት ነዳጅ ማደያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መዉሰዱን አስታዉቋል፡፡
በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ ሐዋሳ ግሎባልና ሐዋሳ ጥቁር ውሃ ኦላ ኢነርጂ ነዳጅ ማደያዎች ከግንቦት 2 እስከ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ነዳጅ ግብይት ሪፖርት የሌላቸው በመሆኑ እርምጃው እንደተወሰደባቸዉ ብስራት ራዲዮ ሰምቷል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ በተደረገዉ የክትትል ሥራ ጥቁር ውሃ ኖክ ቁጥር 2 የነዳጅ ማደያ እጅ በእጅ የነዳጅ ሽያጭ ሲያከናውኑ በማስረጃ በመገኘቱ ፣ ሻሸመኔ ቶታል ቁጥር 3 ሃላባ ማዞሪያ አካባቢ የሚገኝ ማደያ ባልተፈቀደ የነዳጅ ታንከር ወይም በኬሮሲን ታንከር ውስጥ ቤንዚን በመደበቅና በማከማቸታቸዉ እግዱ ተጥሎባቸዋል።
በሌላ በኩል ለሻሸመኔ ሀላባ የመንገድ ፕሮጀክት የተጫነ 4 ተሸከርካሪ ናፍጣ በዚህ ማደያ ውስጥ ያለ ፍቃድ ተራግፎ እየተሸጠ በመገኘቱ ይህ ማደያ እንዲታገድ ሆኗል። በተጨማሪም ሻሸመኔ አፖስቶ ኦላ ኢነርጂ ከመዳረሻ ውጪ ነዳጅ በማራገፍ የአሰራር ክፍተት የተገኘባቸው በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ የነዳጅ ጭነት እገዳ እንደተጣለባቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡