መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 12፤2015-አምስት ወር በፊት እንዲጣሩ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተላኩ የትምህርት ማስረጃዎች እስካሁን ድረስ እንዳልተጣሩ ተነገረ

የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ከአምስት ወር በፊት እንዲጣሩለት ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የላካቸው 158  የትምህርት ማስረጃዎች እስካሁን ድረስ እንዳልተጣሩለት መምሪያው አስታውቋል ።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እንዲጣሩ እፈልጋለሁ ያላቸውን 158 የትምህርት ማስረጃዎች ቢልክም እስካሁን ድረስ ዩኒቨርስቲው የማጣራት ስራ አከናውኖ ማስረከብ እንዳልቻለ ተገልጿል ። ትምህርት መምሪያው ከአሁን ቀደም ለሶስት ጊዜ ያክል ወደ ዩኒቨርስቲው ባለሙያዎችን በመላክ ውጤቱ ከምን እንደደረሰ ለማወቅ እንደሞከረ የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ  አ/ቶ ሽኩራል አወል ከብስራት ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል ።

ነገር ግን የማጣራት ስራው አስቸጋሪ ባይሆንም እስካሁን ድረስ ማጣራት ተደርጎ ውጤቱ እንዳልተሰጣቸው ተገልጿል ። የማጣራት ስራው ለምን እንዳልተሰራ ቢጠየቅም የሚሰጠው ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ ተገልጿል። ዞኑ ከአሁን ቀደም በተያዘው በጀት ዓመት ከጥቅምት ወር ጀምሮ 4 ሺ 4 መቶ 74 የትምህርት ማስረጃዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ልኮ በተደረገ የማጣራት ስራ የ82 መምህራን ሀሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ከነዚህ ውስጥ የተወሰኑ መምህራን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ 67 መምህራን ስራ ጥለው እንደጠፉ ብስራት ሬዲዮ መዘገቡ ይታወሳል ። ዞኑ የጠፉ መምህራን አካባቢ በመቀየር እንዳይቀጠሩ እና እንዲታወቁ የሁሉም መምህራን ስም እንዲለጠፍ መመሪያ መሰጠቱን አ/ቶ ሽኩራን ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል ።

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *