
በአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ቅዱስ ሚካኤል ት/ቤቶች እና ብራስ ዩዝ አካዳሚ የተሰኘ ትምህርት ቤቶች በቀጣይ ዓመት የተማሪዎች ምዝገባ እንዳያከናውኑ ማገዱን አስታዉቋል።ባለስልጣኑ ፤ ማንኛዉም ት/ት ቤት በቀጣይ አመት ለሚያደርገዉ የወርሃዊ ክፍያ ጭማሪ ከተማሪ ወላጆች ጋር ከስምምነት ደርሶ መሆን አለበት ቢልም ፤ ት/ት ቤቶቹ እና ወላጆች ከፍ በሚደረገዉ የክፍያ መጠን ላይ መስማማት አልቻሉም።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራ ለብስራት ራዲዮ እንደተናገሩት ፤ ብራስ ዩዝ አካዳሚ ለቀጣዩ የ 2016 አመት የ 40 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ቢያቅድም ከወላጆች ጋር በተደረገው ዉይይት ተቀባይነት አላገኘም። በአንጻሩ ወላጆች ለቅድመ መደበኛ የ 25 በመቶ እና ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የ 30 በመቶ ለሚደረግባቸዉ ጭማሪ እሺታቸዉን ሰጥተዉ ነበር።
ሆኖም ትምህርት ቤቱ በወላጆች በኩል የቀረበዉን ሀሳብ ዉድቅ አድርጎታል። በዚህም መሰረት የአዲስአበባ የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ሁለቱን አካላት ለማስማማት ጥረት አድርጎ ነበር። በዚህም የ 30 በመቶ የጭማሪ ሀሳብ በባለስልጣኑ ቀርቦ ወላጆችም ከስምምነት ደርሰዉ የነበረ ቢሆንም ትምህርት ቤቱ ሳይቀበለዉ ቀርቷል።
በተመሳሳይ ቅዱስ ሚካኤል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ ዓመት ከ100 እጥፍ በላይ ጭማሪ ለማድረግ ቢያቅድም ከወላጆች ጋር በተደረገዉ ዉይይት 80 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ወስኗል። ሆኖም ወላጆች ከ 50 በመቶ በላይ ጭማሪ ለማድረግ ፈቃደኞች አልሆኑም። ባለስልጣኑ ሁለቱን አካላት በ 60 በመቶ ጭማሪ ለማስማማት ቢሞክርም በተመሳሳይ ትምህትት ቤቱ ዉድቅ አድርጎታል።
በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ በወላጆችና በት/ት ቤቶቹ መካከል ስምምነት አለመደረሱን ተከትሎ ሁለቱም ት/ት ቤቶች ለሚቀጥለዉ አመት የተማሪዎች ምዝገባ እንዳያከናዉኑ ጊዜያዊ እግድ የተጣለባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት ሁለቱም ት/ት ቤቶች ምላሻቸዉን ያሳዉቃሉ ብለዉ እንደሚጠብቁ የተናገሩት ወ/ሮ ፍቅርተ ፤ ከወላጆች ጋር ከስምምነት ይደርሳሉ ብለዉ ተስፋ እንደሚያደርጉ ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።
በበረከት ሞገስ