መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 14፤2015-በኢትዮጵያ የሚገኙ የጥርስ ሃኪሞች ብዛት ከ1500 እንደማይበልጡ ተነገረ

በኢትዮጵያ ቁጥራቸው 1 ሺህ 5 መቶ የሚደርሱ የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ብቻ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ማህበር አስታዉቋል፡፡የማህበሩ የስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ናትናኤል ብርሃኑ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጲያ ያለው የጥርስ ህክምና ስርጭት በዋናነት በከተሞች ላይ ብቻ የተወሰነ ሲሆን በአዲስ አበባ ቁጥራቸው በርከት ብሎ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

እንደ እድገትና ስፋታቸው መጠን  በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች እንዳሏቸው ገልጸው፡፡ቀደም ሲል ምንም አይነት የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ባልነበረባቸው እንደ አፋር፣ ሶማሊ እና ጋምቤላ ባሉ የኢትዮጵያ ክልሎች በመንግስት ሆስፒታሎች ደረጃ የጥርስ ህክምና የተጀመረ ሲሆን ቁጥራቸው እስከ 4 የሚደርሱ የግል  የጥርስ  ክሊኒኮች በሶስቱ ክልሎች ዉስጥ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር የአለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርትም  ሆነ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻር ያነሰ ነው ሲሉ ዶክተር ናትናኤል ብርሃኑ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ገልጸዋል፡፡ ህክምናው በበቂ መልኩ ተደራሽ እንዳይሆን ከማድረጉ በተጨማሪም በባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በተገቢው ሁኔታ የጥርስ ህክምና አገልግሎትን ለዜጎች ለማዳረስ እንዲቻል የጥርስ ህክምና ባለሙያዎችን የማሰልጠን ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡በአሁኑ ወቅት ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት የጥርስ ህክምና ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ማህበሩ ገልጿል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *