በምግብና በስርዓተ ምግብ ትግበራ ማስፋፋት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም የስርዓተ ምግብ ችግርን መፍታት አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ህይወት ዳርስኔ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ህይወት እንዳብራሩት በኢትዮጵያ ከሶሰት በመውለድ የእድሜ ክልል ካሉ ሴቶች ሁለቱ እንዲሁም ከሁለቱ አፍላ ወጣት ሴቶች በአንዷ ወይም ከዛ በላይ የጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ዕጥረት እንዳለባቸው ጥናቶች ያሳያሉ ሲሉ ተናግረዋል። በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ በምግብና በስርዓተ ምግብ ችግሮች ላይ መስራት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በምግብና በስርዓተ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን ተደጋጋሚ በሽታና ሞት በመከላከል ብቻ ሳይሆን በአካልና በአእምሮ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳትን ከማስቀረትና ትምህርት የመቀበል ሁኔታን የማሳደግ ስራን መስራት ዋንኛው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የ2015 ዓ.ም የምግብና የስርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ዓመታዊ የአፈፃጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በትግስት ላቀው