የኢትዮጵያ የወንንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፤ በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በኢትዮጵያ ሙሉወንጌል ቤተ ክርስቲያን ፣ በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሕይወት ብርሃን ቤተ ክርስቲያና እና በኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው አለመግባባት በእርቅ መፍታታቸውን አስታዉቀዋል።
ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም የሁሉም ቤተ እምነት መሪዎች በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቤተ እምነት ህበረቶችና የቤተ ክርስቲያን አጋዥ ድርጅቶች ቀደም ባሉት ዓመታት በወንጌል ስርጭት በኩል ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡና ፍሬያቸውም ጎልቶ የሚታይ ሆኖ በተደራጀ መንገድ ተቀራርበው ይሰሩ እንደነበር በመግለጫው አስታዉሰዋል።
ሆኖም ግን ለልዩነታቸው ምክንያት የሆኑ ቤተ እምነቶቹ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ፥ በተለይም ካውንስሉ ከተመሰረተ በኋላ በቀላሉ ወደ አንድ አሠራር ማምጣትና መግባባት ሳይቻል እንደቆየ በመግለጫው መነሳቱን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል።
በተለይም ካውንስሉ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ ወዲህ የነበሩ ልዩነቶችን ለመፍታት ሰፊ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ጠለቅ ያለ ውይይትና እና ምክክር የሚፈልጉ ከውክልና ፣ ከአደረጃጀት ፣ ከደንብና አሠራር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረስ ሳይቻል ቆይቶ እንደነበር ተጠቅሷል።
ቤተ እምነቶች በጋራ ለልዩነታቸው ምክንያት የሆኑ ተግዳሮቶችን በስፋት ከመከሩ በኋላ ካውንስሉ የተቋቋመበትን ዓላማ መፈጸምና ሀገራዊ ተልዕኮዎችን መወጣት የሚያስችል አቋም እንዲኖረው ለማድረግ የልዩነት ነጥቦችን በመለየት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማስቀመጥ በመቀባበልና በመካከር በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ጣቢያችን ሰምቷል።
በመግለጫው እንደተብራራው ወደፊት በሚደረገው የጋራ እንቅስቃሴ የወንጌል አማኞች ሁሉ ስለተደረገው እርቅ እግዚአብሔርን በማመስገን በጸሎትና በምክር ከካውንስሉ ጎን እንዲሆኑ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው ተጠይቋል።
በአብርሃም ፍቅሬ