መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 10፤2015-በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የእስራኤል ሀኪሞች ቡድን በቀዶ ህክምና መካከል ኤሌክትሪክ በመቋረጡ በእጅ ስልካቸዉ ብርሃን ህክምናዉን ማጠናቀቃቸዉ ተሰማ

በአዲስአበባ የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተገኘ የእስራኤል ሀኪሞች ቡድን በሰኔ ወር መጨረሻ የጭንቅላት እና የአንገት ቀዶ ህክምና ማከናወኑን ገልጿል።በሆስፒታሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የተገኘዉ ይህ የሀኪሞች ቡድን የሶስት አመት ህጻን ለሆነች ታካሚ የቀዶ ህክምና እያከናወነ በነበረበት ወቅት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ እና ጨለማ ላይ ደቂቃዎች እንዳሳለፉ ተሰምቷል።

ሀኪሞቹ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በተቋረጠበት ቅጽበት የእጅ ስልኮቻቸዉን ብርሃን በመጠቀም ቀዶ ህክምናዉን ማጠናቀቃቸዉን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል።ተጠባባቂ ሀይል አምጪ መሳሪያዉ (ጄኔሬተር) ወዲያዉኑ በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባት ባለመቻሉ ሀኪሞቹ ለ 15 ደቂቃዎች የዘለቀ ቀዶ ህክምና የእጅ ስልካቸዉን በመጠቀም እንዳከናወኑ ተሰምቷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ልምድ ያለዉ የሀኪሞች ቡድን አባል የሆኑ ዶ/ር ዮታም ሽኬዲ የተሰኙ ባለሙያ የሀይል መቆራረጡ በአፍሪካ የተለመደ መሆኑን ተናግረዉ ፤ ተጠባባቂ ሀይል ማመንጫዉ በአፋጣኝ አገልግሎት ባለመጀመሩ የእጅ ስልካቸዉን በመጠቀም ህክምናዉን ለማከናወን እንደተገደዱ ጠቅሰዋል። ሀይል እስኪመለስ መጠበቅም በታካሚዉ ህይወት ላይ እንደመፍረድ እንደሚቆጠር ገልጸዋል።

በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ለታካሚዋ ታዳጊ የኤሌክትሪክ ሀይል እስኪመለስ ድረስ እጃቸዉን በመጠቀም አየር እንድታገኝ ጥረት ሲያደርጉ ነበር መባሉን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *