መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 10፤2015-ኢሎን ማስክ ትዊተርን ከገዛ ወዲህ ከማስታወቂያ ይገኝ የነበረው ገቢ በግማሽ ቀንሷል

ትዊተር ባለፈው ጥቅምት በኤሎን ማስክ በ44 ቢሊዮን ዶላር ከተገዛበት ጊዜ አንስቶ ከማስታወቂየ የሚያገኘው ገቢው በግማሽ ያህል እንደቀነሰበት አስታውቋል።በሰኔ ወር ሲጠበቅ የነበረው ያህል የገቢ ጭማሪ እንዳላየ ትዊተር የገለፀ ሲሆን ነገር ግን የሐምሌ ወር “ትንሽ የበለጠ ተስፋ ሰጪ ነው” ብሏል።

ማስክ እ.ኤ.አ በ2022 ወጪን ለመቀነስ ሲሉ ከትዊተር 7,500 ሰራተኞች መካከል ግማሽ ያህሉን አሰናብተዋል። አንዳንድ ግምቶች እንደሚያሳዩት  በፌስቡክ አባት ኩባንያ ሜታ የተከፈተው የትዊተር ተቀናቃኝ ከአሁን 150 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ማግኘቱ ለኢሎን ማስክ ከባድ ትኩሳት ሆኗል ይላሉ።

ከኢንስታግራም ጋር አብሮ የተሰራውና በሜታ የተነደፈው አዲሱ ማህበራዊ መድረክ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ያገኛል ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ተፎካካሪው ትዊተር በከባድ የዕዳ ጫና ውስጥ እየታገለ ይገኛል።

ምንም እንኳን ቢሊየነሩ በማስታወቂያ ገቢ 50 በመቶ ቅናሽ ላይ ከመቼ እስከ መቼ የሚለውን የጊዜ ገደብ ባያስቀምጡም ማስክ በሳምንቱ መጨረሻ እንዳሉት በትዊተር የገንዘብ ፍሰት አሉታዊ ሆኖ ቀጥሏል። ማስክ በትዊተር ገፃቸው ላይ “ሌላ ቅንጦት ከማግኘታችን በፊት አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰት ላይ መድረስ አለብን” ሲሉ አጋርተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ካሰናበቱ እና የክላውድ አገልግሎትን ካቋረጡ በኋላ ማስክ እንዳሉት ትዊተር እ.ኤ.አ. በ 2023 3 ቢሊዮን ዶላር  ገቢን ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ይህው ገቢ ግን በ 2021 ዓመት ካገኘው ከ 5.1 ቢሊዮን ዶላር የቀነሰ ነው።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *