በደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ጨለቆት ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ወላጅ እናቱን በዱላ ደብድቦ ገድሏል በሚል የተጠረጠረዉ የ28 አመት ወጣት በአድራጎቱ የተበሳጩ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ሲያሯሩጡት አምልጦ እጁን ለፖሊስ እንደሰጠ ተገልጿል።
ተጠርጣሪዉ ወላጅ አባቱ በህይወት ሳለ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር የእርሻ መሬት ድርሻዉን በዉርስ አግኝቷል ያለዉ ፖሊስ ከአባቱ የተላለፈለት ይዞታ በኮንትራት መልክ ለሌላ ሰዉ አሳልፎ መሸጡና የእናቱን ድርሻ እኔ ካልተጠቀምኩበት በሚል ልጅ ከእናቱ ጋር ሰጣ ገባዉስጥ ገብቶ ነገሩ ለግጭት እንደዳረጋቸዉ ነዉ የተገለፀዉ።
የእናቱን ይዞታ አርሶ ለመጠቀም ያነሳዉ የእራስ ወዳድነት አጀንዳ እናትየዉ ዉድቅ ማድረጋቸዉ ተከትሎ በነገሩ የተበሳጨዉ የ28 አመት ወጣት እናቱ ላይ የፈረጠመ ጡንቻዉን ሊያሳርፍበሰቸዉ ይሰናዳል።
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ግድም የ 50 ዓመት አዛዉንት እናቱን በዱላ ደጋግሞ ሲያሳርፍባቸዉ ተዝለፍልፈዉ ወድቀዉ ከወደቁበትም ሳይነቁ ህይወታቸዉ አልፏል።
ልጅ ወላጅ እናቱን በዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸዉ የጣር ጩኸት ማሰማታቸዉን ተከትሎ ፈጥነዉ ከወንጀሉ ስፍራ የደረሱት የአካባቢዉ ነዋሪዎች በልጅ እኩይ አድራጎት ተበሳጭተዉ ተጠርጣሪዉ ላይ እርምጃ ለመዉሰድ ሲያሯሩጡት ሸሽቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመዝለቅ እጁን እንደሰጠ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።
በሳምራዊት ስዩም