መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 17፤2015-በቋራ ወረዳ በሚገኘው በርሜል ጊዮርጊስ ገዳም በተከሰተ ወረርሽኝ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

በምዕራብ ጎንደር ቋራ ወረዳ በሚገኘው በርሜል ጊዮርጊስ ገዳም ውስጥ ለፀበል በመጡ ሰዎች ላይ ድንገተኛ ወረርሽኝ መከሰቱን የቋራ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ፀሀፊ እና የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ መልዐከ ገነት ጥበቡ አሻግሬ ለብስራት ሬድዮና ቲቪ ተናግረዋል።

መነሻው የአካባቢ ንፅህና ጉድለት መሆኑ እና በገዳሙ አካባቢ ምንም አይነት መፀዳጃ ቤት አለመኖሩ ለንፅህና ጉድለቱ ምክንያት እንደሆነ በማንሳት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መከሰቱን ገልፀዋል።

መፀዳጃ ባለመኖሩ አብዛኛው ሰው በገዳሙ ዙርያ ባለ ሜዳ ላይ እንደሚፀዳዳ እና ቦታው በረሀማ እንደመሆኑ  አሁን ላይ ካለው የክረምት ወቅት ጋር ተዳምሮ ምቹ የአካባቢ ንፀህና እንዳይኖር እንዳደረገው ተናግረዋል።

የወረርሽኙ ሁኔታ እስኪጣራ መንገድ ክፍት እንዳልነበር ገልፀው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ አራት መጠለያዎች ውስጥ 1500 የሚሆኑ ሰዎች መጠለላቸውን ገልፀዋል።

ከተጠለሉት 1ሺ500 ሰዎች ውስጥ ግን ሁለት ሰዎች በተከሰተው ወረርሽኝ ህይወታቸው እንዳለፈም ተናግረዋል።

ከሀምሌ 14 2015 ዓ.ም ጀምሮ ግን መንገድም እንደተከፈተና መንግስትም የተለያዩ የህክምና ክትባቶችን በማዘጋጀቱ  በታማሚዎች ላይ ለውጥ መኖሩን እንዲሁም የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከትም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ፀበልተኞቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየተገናኙ እና ወደ መጡበት አካባቢም በሰላም በመመለስ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *