መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 18፤2015-የኢትዮጲያ በ2015 ዓመት ከአህያ ስጋ የወጪ ንግድ 3 መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ አገኘች

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የአህያ ስጋን ወደ ሆንግኮንግ በመላክ 3 መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ገቢ ማግኘቷን የእንስሳት ልማት ኢንስትቲዩት አስታውቋል፡፡በኢንስትቲዩቱ ምክትል ዋና  ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሳህሉ ሙሉ በተለይ ከብስራት ሬድዮና ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ከአህያ ስጋ ውጪ የአህያ ቆዳን እንደ ቻይና ያሉ ሃገራት ለመድሃኒትነት በስፋት ሲጠቀሙበት የሚስተዋል በመሆኑ የስጋ ምርቱን ወደ ሆንግኮንግ እንዲላክ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ገቢው  የተገኘውም በተጠናቀቀው በጀት አመት 140 ቶን የአህያ ስጋ ምርትን ወደ ውጪ ገበያ በመላክ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡በበጀት አመቱ 6 መቶ ቶን የአህያ ስጋን ወደ ውጪ ለመላክ አስቀድሞ ታቅዶ እንደነበር ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በአህያ ስጋ የወጪ ንግድ  ዙሪያ የቄራ ድርጅቶች የማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት የነበረባቸው  በመሆኑ ምርቱ ከአመቱ አጋማሽ በኃላ ለአለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲኖረው አስገዷል፡፡ይኸው ችግር በዘንድሮው አመት በታቀደው ልክ ገቢ እንዳይገኝ ያደረገ ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፏ ከተስተዋለው የማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት አኳያ በዘንድሮ በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ተገኝቷል የተባለ ሲሆን ባለፈው በተመሳሳይ ወቅት ከአህያ ስጋ የውጪ ንግድ ሽያጭ 2 መቶ ሺህ ገደማ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቶ እንደነበር ዶክተር ሳህሉ ሙሉ አስታውሰዋል፡፡በተጠናቀቀው የ2015 በጀት አመት  ከአህያ ስጋ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢም ከአምና  ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ እንዳለው ያሳያል፡፡

ከማጓጓዣ ኮንቴይነር እጥረት ጋር በተያያዘ ያለውን  ችግር ለመፍታትም ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር  ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎች በመሰራታቸው እና ለቄራ ድርጅቶች አስፈላጊው ግብአት እንዲሟላላቸው በመደረጉ ከአህያ ስጋ የወጪ ንግድ የተሻለ ውጤትን ማግኘት ተችሏል፡፡በሚቀጥሉት ዓመታት ከዘርፏ የተሻለ ገቢን ለማግኘትና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያስችሉ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት ታቅዷል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሳህሉ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮና ቲቪ ተናግረዋል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *