
በሰሜን ምዕራባዊ ፓኪስታን በነበረ የፖለቲካ ሰልፍ ላይ በደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ቢያንስ 44 ሰዎች ሲገደሉ 200 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የፓኪስታን መንግስት ባለስልጣናት ገልጸዋል። ፍንዳታው የደረሰው በትላንትናው እለት ወግ አጥባቂው ጃሚያ ፓርቲ ፓኪስታንን ከአፍጋኒስታን ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ በሚገንው ጃውር አውራጃ ላይ በነበረ የፖለቲካ ሰልፍ ነው።
ለጥቃቱ ወዲያው ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።የክልሉ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው አጥፍቶ ጠፊው በርካታ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተቀመጡበት መድረክ አካባቢ ያጠመደው ፈንጂ እንዳፈነዳው ገልጿል። የመጀመርያ ምርመራዎች እንዳሳዩት ከሆና የአይኤስ ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ ሊኖር እንደሚችል እና የፖሊስ መኮንኖች አሁንም ምርመራ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የታጠቀው ቡድን አይኤስ የፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ መንግስት ከወደቀ በኋላ በጎረቤት አፍጋኒስታን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። የአፍጋኒስታን የታሊባን አስተዳደርን የሚቃወም ሲሆን ተራራማ ድንበር አቋርጠው በፔሻዋር አካባቢ በመደበቅ የሚታወቁ አባላት አሉት።
የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የፓኪስታን መንግስት ባለስልጣናት እንደተናገሩት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል 15ቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።ከጥቃቱ በስተጀርባ ያለው ዓላማ እስካሁን ግልጽ አይደለም.።የጸጥታ ሃይሎች አካባቢውን ከበው የፍንዳታው ምርመራ ማካሄዳቸውን ግን ቀጥለዋል።
በስምኦን ደረጄ