መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 2፤2015-የኒጀር ወታደራዊ መንግስት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመ

የኒጀር ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱራህማን ቲቺያኒ የቀድሞ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።አሊ መሃማን ላሚን ዘይኔ በመፈንቅለ መንግስቱ ወቅት በአውሮጳ የነበሩትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃማዱ ኡሁሙዱ ተክተዋል።

በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንዳሉ የተዘገበው ዘይኔ ከ2001 ጀምሮ የካቢኔ ዳይሬክተር እና የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው የሰሩ ሲሆን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ማማዱ ታንጃ በ2010 በጦር ኃይሉ እስኪወገዱ ድረስ በኃላፊነት ነበሩ። ሹመቱ የተገለፀው ትላንትና ምሽት የመንግስት ቃል አቀባይ በሆነው ቴሌ ሳህል በተሰኘው የመንግስት የቴሌቭዥን ጣቢያ ባስነበበው መግለጫ ነው።

ዘይኔ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻድ፣ በአይቮሪ ኮስት እና በጋቦን በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ ሰርቷል ሲል የግል መገናኛ ብዙሃን የሆነው አክቱኒገር የዜና ድረ-ገጽ ዘግቧል። በተመሳሳይ በትላንትናው እለት ወታደራዊው መሪ ብርጋዴር ጄነራል አማዱ ዲዲሊ የሀገሪቱ የሰላም ማጠናከር ከፍተኛ ባለስልጣን መሪ ተደርገው የተሾሙ ሲሆን ብርጋዴር ጄኔራል አቡ ታግ መሃማዱ የጦር ኃይሉ እና የብሄራዊ ጄንዳርሜር ዋና ኢንስፔክተር ተደርገው ተሹመዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *