
???????? በጦርነቱ ወቅት ፤ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ምስረታ ካፒታልን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደጉ ለግዕዝ ባንክ ምስረታ ሌላ ፈተና ፈጥሯል
ግዕዝ ባንክ በ 2012 ዓ.ም ከብሔራዊ ባንክ የመደራጀት ፈቃድ ካገኘ በኋላ በወቅቱ የነበረዉን የባንክ ማደራጃ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር አሟልቶ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በተከሰተው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የምስረታ ሂደቱ መስተጓጎሉን የግዕዝ ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ም/ል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ቶማስ ሀይሉ ለብስራት ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ባንኩ ከ 13 ሺህ 800 በላይ ባለአክሲዮኖቹ ፤ 850 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ፣ 1.8 ቢሊዮን የተፈረመ ካፒታል እና 1.4 ሚሊዮን ዶላር በዉጪ ሀገራት ከሚገኙ ባለአክሲዮኖች መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። ሆኖም በወቅቱ የባንክ ማደራጃ ካፒታል በ 10 እጥፍ በመጨመሩ ባንኩ የመደራጃ መንገዱን እንዳስተጓጎለበት አክለዋል። ይህም በርካታ በመደራጀት ላይ የነበሩ ባንኮችን ከስራዉ እንዲወጡ እንዳደረጋቸዉም ጠቅሰዋል።
ባንኩ ለመደራጀት ቀሪ የሚያስፈልገዉን የገንዘብ መጠን ለመሙላትም በአዲስ መልኩ አክሲዮን መሸጥ መጀመሩን አስታዉቋል። ባንኩ ትናንት እሁድ ነሃሴ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከባለድርሻ አባላት ጋርም ዉይይት አካሂዷል።
በዚህም ዝቅተኛ መግዛት የሚቻለዉ የአክሲዮን ዋጋ 100 ሺህ ብር ከፍተኛ ደግሞ 250 ሚሊዮን ብር መሆኑን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ገልጿል። አቶ ቶማስ ፤ ማህበረሰቡ ካለበት ችግር አንጻር የዝቅተኛ አክሲዮን መግዣ ዋጋዉ አሁን ያለዉን ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ ነዉ ወይ ሲል ጣቢያችን ላቀረበላቸዉ ጥያቄ በምላሻቸዉ ፤ አክሲዮን ገዢዎች ቅድሚያ የስራ ማስኬጃዉን 25 በመቶኛዉን ከከፈሉ በኋላ ቀሪዉን በቁጠባ መልክ በጊዜ ሂደት መክፈል የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋታቸዉንም ገልጸዋል።
የአደራጅ ኮሚቴዉ ም/ል ሰብሳቢ ፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ያለዉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተለይም የጥሬ ገንዘብ እጥረት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል እድገት እንዳያሳይ እንቅፋት መሆኑንም ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በበረከት ሞገስ