መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 16፤2015-የዋግነር አለቃ ፕሪጎዝሂን ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቪዲዮ መልዕክት አስተላለፉ

የዋግነር አለቃ ዬቭጄኒ ፕሪጎዝሂን በሩሲያ ከተቃጣው የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ አድራሻቸው ታይተዋል።በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ጥቆማ ሰጥተዋል። ቪዲዮው የት እንደተቀረፀ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ከዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ጋር በተገናኘ የቴሌግራም ገፅ ላይ በተጋራ ቪዲዮ ላይ ፕሪጎዝሂን በውጊያ ቀጠና ውስጥ እንዳሉ ያሳያል፣ ቡድኑ አፍሪካን የበለጠ ነፃ እያደረገ ስለመሆኑ አክለዋል። ዋግነር በአህጉሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች እንዳሉት ይታመናል።

የፕሪጎዝሂን ወታደሮች ማሊ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ጨምሮ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የመብት ተሟጋቾች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ብለው በሚከሷቸው አገሮች ውስጥ ይገኛሉ።ዩናይትድ ኪንግደም ባለፈው ወር በመካከለኛው አፍሪካ በሁለቱ የዋግነር ኦፕሬሽን ኃላፊዎች ላይ በሲቪል ዜጎች ላይ ማሰቃየት እና ግድያ ፈፅመዋል በሚል ክስ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።

የዋግነር ተዋጊዎችም በአህጉሪቱ ራሳቸውን በህገ ወጥ የወርቅ ስምምነቶች በማበልጸግ ወንጀል በአሜሪካ ተከሰዋል። በቪዲዮው ላይ ፕሪጎዝሂን ዋግነር በማዕድን ፍለጋ እንዲሁም ታጣቂዎችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን በመዋጋት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ፍትህ እና ደስታ  ለአፍሪካ ህዝቦች ለታጣቂዎችና ለሌሎች ሽፍቶች ህይወትን ቅዠት እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ፕሪጎዝሂን በሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ ባለፈው ወር የአፍሪካ-ሩሲያ የመሪዎች ስብሰባ ላይ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የፕሬዝዳንት አማካሪ አምባሳደር ፍሬዲ ማፑካ ሲጨባበጡ ፎቶግራፍ ተነስተው ነበር።

ፕሪጎዝሂን ለ24 ሰአታት ብቻ የፈጀውን የአጭር ጊዜ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በኃላ ከህዝብ እይታ ተሰውረው ቆይተዋል። በወቅቱ ወደ 5,000 የሚጠጉ የዋግነር ወታደሮች የደቡብ ሩሲያን የሮስቶቭ ኦን-ዶን ከተማ ተቆጣጥረው ወደ ሞስኮ በመጓዝ ወታደራዊ አመራሩን ለማስወገድ መሞከራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ፕሪጎዝሂን ከክሬምሊን አለቆች ጋር በቤላሩስ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሽምግልና ድርድር ከተደረገ በኃላ እርቅ ወርዷል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *