መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 23፤2015-ለአቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት ቀን ንግሥ በዓል ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም የሚያቀኑ ምዕመናን በምሽት ጉዞ እንዳያደርጉ ተጠየቀ

ለአመታዊዉ የአቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት ቀን ንግሥ በዓል ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም የሚያቀኑ ምዕመናን በምሽት ጉዞ እንዳያደርጉ የአቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም አስተዳዳሪ አባ ፍቅረማርያም ተከስተ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በየዓመቱ ነሃሴ 24 ቀን በሚከበረዉ በዚህ ንግሥ በዓል በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ገዳሙ እንደሚያቀኑ የጠቀሱት የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ፍቅረማርያም ፤ በአካባቢው ያለዉን የጸጥታ ሁኔታ በመስጋት ዘንድሮ ለክብረ በዓሉ የሚገኙ ምመናን ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ገምተዋል። 

እንደ አስተዳዳሪዉ ገለጻ ፤ ምዕመናን ከምሽት 1 ሰዓት በኋላ ጉዞ እንዳያደርጉ መክረዋል። በዘንድሮው የንግሥ ክብረበዓልም እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ምዕመናን ይገኛሉ ብለዉ እንደሚጠብቁ አክለዋል።

የደብረሊባኖስ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ብርሃኑ ሌንጮም ይህንኑ በመግለጽ ምዕመናን በሌሊት ከሚደረጉ ጉዞዎች እንዲጠበቁ አሳስበዋል። የወረዳዉ ፖሊስ ከሱሉልታ ጀምሮ ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ጋር በትስስር የመንገዱን ደህንነት እንደሚያስጠብቁም ለጣቢያችን ተናግረዋል። ሆኖም የሌሊት ጉዞዎች ከደህንነት አኳያ እንደማይመከሩ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪነትም ሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መጨናነቅ እንዳይፈጠር ቦታ መዘጋጀቱን ፣ የክረምት ወቅት እንደመሆኑ አሽከርካሪዎች ጠምዝማዛ እና ገደላማ በሆኑ አካባቢዎች በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ እና በክብረ በዓሉ ለሚከሰቱ ማንኛቸዉም የማጭበርበር እና የስርቆት ድርጊት አፋጣኝ ችሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸዉንም ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የደብረሊባኖስ ገዳም ከአዲስአበባ 105 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የተመሰረተዉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በጻድቅነት በሚታመኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በ 1300ዎቹ መጀመሪያ እንደሆነ ይነገራል። ገዳሙ “ዳግማዊ እየሩሳሌም” በመባል የሚጠራም ሲሆን በዉስጡ ወንድና ሴት ደናግል መናኞች እንዲሁም ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራ ዋሻ ያለዉ ነዉ።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *