መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 29፤2015-በኢቱር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል

ቅዳሜ ሌሊት 9:50 በአዳማ መቂ መገንጠያ በሚገኘዉ ኢቱር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአንድ ሰዉ ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በእሳት አደጋዉ በመጋዘን ዉስጥ ተከማችቶ የነበረ ጥሬ ዕቃና ለሽያጭ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ ዉጤቶች መውደማቸውን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ እሳት አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽንና የአዳማ ከተማ እሳት አደጋ ክፍል እንዲሁም የደረቅ ወደብ እሳት አደጋ ተከላካይ ክፍሎች እሳቱ ወደፋብሪካዉ ተዛምቶ ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል ችለዋል።

እሳቱን ለመቆጣጠር ስምንት የዉሀ ቦቴዎች 64 ጊዜ ምልልስ በማድረግ  ለእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ዉሀ ማቅረብ ችለዋል።

የእሳት አደጋዉ ሲያጋጥም ፋብሪካዉ በስራ ላይ የነበረ ሲሆን በርካታ የፋብሪካዉ ሰራተኞች ከአደጋዉ ማምለጥ ችለዋል ፤ ዕድሜዉ 26 ዓመት የተገመተ ወጣት ህይወቱ ያለፈው እና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸዉ አራቱ ሰዎች በመጋዘን አረፍ ብለው እንደነበረም ተነግራል።

የእሳት አደጋዉ ቅዳሜ ለሊት 9 ሰዓት ከ50ላይ መነሳቱን ጨምረው የነገሩን አቶ ንጋቱ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የተቻለው እሁድ ነሀሴ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 12: 20 ሰዓት መሆኑን አንስተዋል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *