መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 3፤2016-በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ቀናት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት አልፏል

በኦሮሚያ ክልል በ2015 ዓመት ከጷጉሜ አንድ ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ  ቀናቶች 9 የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል።

ከአደጋዎቹ መካከል በሰባቱ ሞት የተመዘገበባቸው ሲሆን ሁለቱ  ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት  ያደረሱ መሆናቸውን በኦሮሚያ ክልል የትራፊክ ቁጥጥር እና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ኮማንደር በላቸው ትኬ  ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በተመዘገበው ሰአደጋ የአስር ሰዎች ህይወት አልፏል ። በተመሳሳይ አስር ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት የደረሰ መሆኑ ተገልጿል ። አደጋዎቹ በምዕራብ ሀረርጌ ፣  በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ  ፣ ቡሌ ሆራ ከተማ  እና በክልሉ የተለያዩ ክፍሎች  የደረሱ ናቸዉ።

የአደጋዎቹ  መንስኤዎቹ ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ፣በቂ እረፍት ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ርቀትን ጠብቆ አለማሽርከር እንዲሁም አሽከርካሪዎች እርስ በእርስ በመሽቀዳደም መሆኑን ተገልጿል ።

በአጠቃላይ በደረሱ አደጋዎች የወደመው ንብረት 700 ሺህ ብር የሚገመት መሆኑም ተገልጿል ። በበዓል ቀናት ምንም አይነት አደጋም አልተፈጠረም ።

አሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ እና ጠጥተዉ እንዲሁም በመሽቀዳደም ማሽከርከራቸው በማቆም የሰዉን  ህይወት  ከመቅጠፍ እንዲጠነቀቁ አሳስበዋል። እግረኞች በተቻላቸዉ አቅም ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸዉን ከትራፊክ አደጋ እንዲጠብቁ ሲሉም ኮማንደር በላቸው ተኪ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *