በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ለ15 ዓመታት ግብር ያልከፈለ ግለሰብ በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጣ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ።
ነዋሪነቱ በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ጫሬ ዶቄ ቀበሌ የሆነ አደለ ሚኖታ የተባለ ግለሰብ በስሙ ተመዝግቦ የሚገኝ አንድ ሄክታር የእርሻ መሬት በዓመት 20 ብር የሚከፈል ግብር ለ15 ዓመታት ሳይከፍል መቆየቱ ተገልጿል ።
በዚህም ከ2000 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ያልከፈለውን የእርሻ መሬት ግብር እና ቅጣቱን ጨምሮ 375 ብር እንዲከፍል በተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦለት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።
ግለሰቡ እንቢተኛ ስለመሆኑ ለአመያ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ታክቲክ ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ በተፃፈ ደብዳቤ መነሻ ምርመራ ያጣራው የአመያ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማስረጃ የምርመራ መዝገቡን አደራጅቶ ለዐቃቤ ህግ መዝገቡን መላኩ ተጠቅሷል ።
የምርመራ መዝገቡን የተቀበለው ዐቃቤ ህግ ግብር ባለመክፈሉ በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት እንዳቀረበው ተገልጿል ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ ለ15 ዓመታት ግብር ሳይከፍል የቆየውን ግለሰብ ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል ፡፡
በዚህ መሰረት የአመያ ዙረያ ወረዳ ፍርድ ቤት በተከሳሽ አደለ ሚኖታ በ8 ወር እስራትና በ1000 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል ።
በአበረ ስሜነህ