መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 4፤2016-ፑቲን እና ኪም እርስ በርስ የሽጉጥ ስጦታ እንደተለዋወጡ ተነገረ

የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሩሲያ የጠፈር ማእከል ሲገናኙ የጠመንጃ ስጦታ እርስ በእርስ መሰጣጠታቸውን ክሬምሊን የገለፀ ሲሆን የሩሲያው መሪ ለፒዮንግያንግ አቻቸው ከኮስሞናውት የጠፈር ልብስ ጓንት ሰጥተዋቸዋል።

ከሰሜን ኮሪያ በመነሳት ጥይት በማይበሳው ባቡሩ ተሳፍረው ረቡዕ እለት በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ አሙር ክልል በሚገኘው ቮስቴክኒ ኮስሞድሮም የገቡት ኪም ከፑቲን ጋር ለ40 ሰከንድ ያህል በመጨባበጥ ሞቅ ያለ ሰላምታ መለዋወጣቸው ይታወሳል።የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሁለቱ መሪዎች ስጦታ ተለዋውጠዋል ወይ ተብለው ሲጠየቁ ፑቲን ለኪም ከፍተኛ ጥራት ያለው ሩሲያ ሰራሽ የሆነ ጠመንጃ እና ጓንት እንዲሁም በህዋ ላይ ብዙ ጊዜ የሚለበሰውም የጠፈር ልብስ ሰጥቷቸዋል ብለዋል።

በምላሹም ኪም ለፑቲን በሰሜን ኮሪያ የተሰራ ሽጉጥ ከሌሎች ስጦታዎች ጋር አበርክተዋል ሲሉ ፔስኮቭ ተናግረዋል። ፑቲን በሩስያ ገጠራማ አካባቢ ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ከቤት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ለብዙ አመታት ሲሳተፉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች የሚጋሩ ሲሆን የጫካ አደን ላይ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል።

በተጨማሪም ፑቲን የሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግን ለመጎብኘት የኪምን ግብዣ “በአመስጋኝነት መቀበላቸውን” የሰሜን ኮሪያ መንግስታዊ ቴሌቪዥን አስቀድሞ ያስታወቀውን ዘገባ ፔስኮቮ እውነት ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።ቃል አቀባዩ ፔስኮቭ እንደተናገሩት የፑቲን ጉብኝት ከመዘጋጀቱ በፊት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን ወደ ፒዮንግያንግ በመላክ በፍጥነት ሂደቱ ይዘጋጃል ሲሉ አክለዋል።

ጉብኝቱ የፑቲን ሁለተኛው ጉዞ ወደ ሰሜን ኮሪያ ይሆናል። ለመጨረሻ ጊዜ ፑቲን ወደ ሰሜን ኮርያ ያመሩት የኪም ወላጅ አባት ኪም ጆንግ ኢልን ለፕሬዚዳንትነት በተመረጡ ከጥቂት ወራት በኋላ ከ23 ዓመታት በፊት ነበር። ኪም ለመጨረሻ ጊዜ ሩሲያን የጎበኙት እ.ኤ.አ. በ2019 እንደነበር ይታወሳል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *