መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 8፤2016-በሚዛን አማን ከተማ ለሁለተኛ ሚስቱ አድልቷል በሚል የስድስት ልጆቿን አባት በስለት ቆርጣ የገደለችውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ ቀበሌ ቀጠና 3 ልዩ ስፍራው ኮመታ ተብሎ በሚጠራበት አካባቢ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት 30 ሰዓት ላይ ነው።

የ22 አመት ትዳር አጋሯንና የስድስት ልጆቿን አባትና በስለት አንገቱን በመቁረጥ የገደለችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሏን  የሚዛን አማን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፒክተር አዳነ አለማየሁ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ፡፡

ፖሊስ ግለሰቧን በቁጥጥር ስር በማዋል ባደረገው ቅድመ ምርመራ ለ22 አመታት በትዳር መቆየታቸውንና ሁለት ወንድና አራት ሴቶችን በአጠቃላይ ስድስት ልጆችን መውለዳቸውን ገልጿል።ከሶስት አመታት በፊት ሌላ ትዳር መስርቶ ሁለተኛ ሚስት በማግባት ለሁለተኛ ሚስቱ በብዛት ያዳላል የሚል ቅሬታ በውስጧ መፈጠሩን ተነግሯል፡፡

በዚህም  መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽቱን ሰክሮ በመምጣቱ እና በ50 ብር የገዛሁትን ጎመን ረግጧል በሚል የተበሳጨችው ሚስት ጉሮሮውን በማነቅ መሬት ላይ በመጣል ጎመን በምትከትፍበት  ቢላዋ አንገቱን በመቁረጥ ህይወቱ እንዲያልፍ  ማድረጓ ተረጋግጧል፡፡

ግለሰቧ በፈፀመችው ግድያ ተጨማሪ ምርመራ እየተጣራባት ሲሆን የምርመራ መዝገቡ እንደተጠናቀቀ ክስ እንዲመሰረትባት ለዐቃቤ ህግ እንደሚላክ ረዳት ኢንስፒክተር አዳነ አለማየሁ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *