መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 14፤2016-በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ህንፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከህንፃ ለመዝለል የሞከሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

በአዲስ አበባ ከተማ ቅዳሜ ምሽት 2 ሰዓት ገደማ ላይ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 የረር የገበያ ማዕከል ህንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ በአምስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የእሳት አደጋው የተነሳው በገበያ ማዕከሉ ሁተለኛ ፎቅ ላይ ካሉ የንግድ ሱቆች ላይ ሲሆን በእሳት አደጋዉ እንድ የሙሽራ ልብስ ማከራያ ቤት ፣ ሬስቶራንትና እንዲሁም አንድ የፎቶ ስቲዲዮ ላይ ጉዳት ማድረሱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

በእሳት አደጋዉ ጉዳት ከደረሰባቸዉ መካከል የእሳት አደጋ ሰራተኛና የፖሊስ አባል ሲሆን ቀሪዎቸ ሶስት ሰዎቸ በህንጻው የሆቴል አገልግሎት በሚሰጥበት 4 ኛ እና 5 ኛ ፎቅ ላይ አልጋ ተከራይተዉ የነበሩ መሆናቸው ተገልፃል።የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ በሰዉና በንብረት ላይ ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል።

በህንጻዉ አልጋ ተከራይተዉ የነበሩ ሶስት ሰዎች በተፈጠረዉ የእሳት አደጋ ተደናግጠዉ ከህንጻዉ ዘለዉ ለመዉረድ ሙከራ እያደረጉበት ባለበት ሰዓት የእሳት አደጋ ስራተኞች ደርሰዉ ህይወታቸዉን ማትረፍ መቻሉን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል  ምሽት  4:29 በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዳትሰን ሰፈር በአንድ መኖሪያ ቤት እንዲሁም ሌሊት 9:50 በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በዳቦ መጋገሪያ ቤት ላይ የእሳት አደጋ አጋጥሞ መጠነኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እሳቱን በቀላሉ መቆጣጠር ችለዋል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *