መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 15፤2016-በትራኮን ሪል እስቴት ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር አስር ሰዓት ወስዷል

???? በእሳት አደጋው ወቅት ሁለት የአደጋ ግዜ ሰራተኞች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንዱ ከህንፃ ወድቋል

በአዲስ አበባ ከተማ ትላንት መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1:05 ሰዓት ላይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሀጫሉ ሁንዴሳ መንገድ ትራኮን ሪል እስቴት እየገነባ ባለዉ አፓርታማ  5ኛና 6ኛ ፎቅ ላይ የተነሳዉ የእሳት አደጋ ለሊት 10 ሰዓት በቁጥጥር ስር መዋሉን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በእሳት አደጋው በሁለት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ሲያደርስ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።

አደጋዉ የደረሰባቸዉ ሁለቱም  የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሲሆኑ  አንደኛዉ ሰራተኛ እሳቱን በማጥፋት ሂደት ከህንጻዉ ላይ ወድቆ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በአሁን ሰዓት በአለርት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ይገኛል።

የእሳት አደጋዉ  በአካባቢዉ ባሉ  መኖሪያ ቤቶች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን  እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 9 ሰዓት መፍጀቱን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር የዉሀ ቦቴዎችን ጨምሮ 18 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች ከ94 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል።የአዲስ አበባ መንገዶችና የአዲስ አበባ ዉሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ዉሀ የጫኑ ቦቴዎችን በማቅረብ ድጋፍ አድርገዋል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *