መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 21፤2016 – በግሸን ደርበ ከርቤ የንግስ በዓል 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ታድመዋል ተባለ

በየአመቱ መስከረም 21 ቀን የሚከበረዉ የግሸን ደርበ ከርቤ የንግስ በዓል በዛሬዉ እለት በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን መኳንንት ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

እንደ ሃላፊዉ ገለጻ ፤ በዚህ አመት ክብረበዓል 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ተገኝተዋል ያሉ ሲሆን ይህም ከአምናዉ እና ከዚህ ቀደም ከታደሙ ሰዎች ቁጥር መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸዋል።

ምዕመናን የአፋር መስመርን አማራጭ መንገድ በመዉሰድ እንዲሁም የአየር ትራንስፖርትን በመጠቀም በክበረ በዓሉ መታደማቸዉን ጠቅሰዋል። ተጓዦች ለተጨማሪ ወጪዎች ቢጋለጡም የባህልና ቱሪዝም ቢሮዉ ግን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ገቢ ሊያገኝበት እንደሚችል አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

በዞኑ የኮሌራ ወረርሽኝ በመኖሩ የጤና ቢሮዉ በሽታዉን ከመከላከል አኳያ የጤና ባለሙያዎችን አሰማርቶ ዉሃ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት እንዲታከም ማድረጉን ተናግረዋል። በሌላ በኩል የጸጥታ ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም አገልገሎቶች መስተጓጐል እንዳይፈጥሩ ተሰርቷል ነዉ ያሉት።

በዓሉም በዛሬዉ እለት ካለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን መኳንንት ጨምረው ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *