መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 23፤2016 – በጅማ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪ ፤ በተሽከርካሪዉ ዉስጥ ወድቆ ያገኘዉን 17 ሺህ ብር ለባለቤቱ መለሰ

በጅማ ከተማ አስተዳደር ወረዳ ሁለት የባለሶስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪ የሆነዉ አቶ ሲሳይ ሽጉጤ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተሽከርካሪዉ ዉስጥ ተረስቶ የነበረ በፌስታል የተጠቀለለ 17 ሺህ ብር ማግኘቱን ለፖሊስ ሪፖርት ካቀረበ ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ የገንዘቡ ባለቤት በመገኘቱ ተመልሷል ነዉ የተባለዉ።

አሽከርካሪዉ ተሳፋሪዎቹን በየቦታቸዉ ካደረሰ በኋላ ተራ በመጠበቅ ላይ እያለ ገንዘቡን መመልከቱን ተናግሯል። በመቀጠለም ገንዘቡን ለፖሊስ ማስረከቡን ገልጿል።

የወረዳዉ ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ኮማንደር ሙሉጌታ ተክሌ እንደነገሩን ፤ ፖሊስ በተለያዩ የመገናኛ አዉታሮች የገንዘቡን ባለቤት በማፈላለግ ላይ መቆየቱን አንስተዋል። ማስታወቂያዉ ዘግይቶ የደረሳቸዉ አቶ አብርሃም አባ ቡልቡ ፤ ገንዘባቸዉ መጥፋቱን አምነዉ ተቀብለዉ የነበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በትናንትናው እለትም ፖሊስ የጠየቀዉን ማስረጃ ግለሰቡ በማቅረባቸዉ ገንዘቡ ተመላሽ ሆኖላቸዋል ሲሉ ኮማንደር ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። ፖሊስ አሽከርካሪዉ ለፈጸመዉ ተግባር የታማኝነት የምስክር ወረቀት የሰጠዉ ሲሆን የገንዘቡ ባለቤትም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *