መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 23፤2016 – “ከፈጣሪ ትዕዛዝ ተሰጥቶኛል” ያለ ፓስተር የጊምቢቹን ከተማ ስያሜ ለመለወጥ ሲያደርገዉ የነበረዉ ጥረት በከተማ አስተዳደሩ እንዲቋረጥ ተደረገ

“ረዕይ ታይቶኛል” ያለ አንድ የሀይማኖት መምህር በሀድያ ዞን የምትገኘዉ የጊምቢቹ ከተማን ስያሜ ለመለወጥ ሲያደርግ የነበረዉ ጥረት እንዲቋረጥ መደረጉን የከተማ መስተዳድሩ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ አብነት ሞገስ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የሀይማኖት መምህሩ አርፊጮ የሚባል የቤተ-እምነት መሪ ሲሆን  4 ወራትን ጾም ጸሎት በመያዝ ካሳለፈ በኋላ “ራዕይ ታይቶኛል ከፈጣሪም ትዕዛዝ ተሰጥቶኛል” በሚል የጊሚቢቹ ከተማ ስያሜን “ኤንጃሜ” በሚል ቀይሯል ነዉ የተባለዉ።

ለዚህም ደግሞ ጊምቢቹ የሚለዉ መጠሪያ ነዋሪዉን የማይወክል ነዉ በሚል ለመለወጥ እንዳነሳሳዉ አቶ አብነት ተናግረዋል።ይህም በቤተ እምነት ተቋሙ አንዳንድ ተከታዮች በኩል ተቀባይነት ያለዉ ጉዳይ ነዉ ያሉት አቶ አብነት ፤ ሆኖም የከተማዉ ነዋሪም ሆነ መስተዳድሩ በዚህ የስም ቅያሪ እንደማይስማማ ተናግረዋል። የከተማዋን ስያሜ ለመወለጥ ቢፈለግም በከተማዉ ም/ቤት ቀርቦ ድምጽ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል።

መምህሩ አዲስ ለከተማዋ የሰጠዉ ስያሜ በቅድሚያ በቤተ እምነት ተቋሙ አካባቢ የጀመረ ሲሆን በኋላ ታፔላ እና ባነር እንዲሁም ባንዲራ ጭምር በማሰራት በወጣቶች ማዘዉተሪያ ላይ ለጥፏል ብለዋል።  ከዚህም ድርጊት በኋላ ነዋሪዉ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃዉሞዉን በማሰማቱ የከተማዋ ከንቲባ በተገኙበት ድርጊቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል ብለዋል።

በዛሬዉ እለትም የእምነት ተቋሙን መሪ እና ተከታዮች የከተማ መስተዳድሩ ተወካዮች ችግሩን በንግግር ለመፍታት መወያየታቸዉን አቶ አብነት ጨምረዉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *