መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 25፤2016 – በሮቤ ከተማ የ15 ዓመት ታዳጊን አስገድደው በመድፈር በካሜራ ቀርፀንሻል እንዳታጋልጪን ሲሉ የነበሩ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

በባሌ ዞን በሮቤ ከተማ ወረዳ 1 መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በስልክ በመጥራት የአስገድዶ መድፈር የፈፀሙ ሁለት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸው የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮምኒኬሽን እና ሚዲያ ባለሙያ ሳጅን ጎሳ ስንታየው ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት አንደኛ ተከሳሽ አማኑ ዋርሳ እና ሁለተኛ ተከሳሽ አብድለሀድ ቻቦ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ድርጊቱን እንደፈፀሙት ተናግረዋል።

የ15 ዓመቷን ልጅ በስልክ ቤታቸው ድረስ ጠርተው ካስገቡ በኃላ እንዳትጮህ እና የሰው እርዳታ እንዳታገኝ አፏን በፕላስተር አሽገው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደፈፀሙባት መረጋገጡንም ገልፀዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች ተጎጂዋ ለቤተሰቦቿ እና ለህግ አካላት የደረሰባትን ድርጊት ከተናገረች በቪዲዮ የቀረጿትን በማህበራዊ ድህረገፅ እንደሚለቁት ሲያስፈራሯት እንደነበርም ከተገኘው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ተጎጂዋ የደረሰባትን ጉዳት ደብቃ እያለች በደረሰባት የጤና ችግር ሮቤ ጤና ጣቢያ ስትመረመር የመደፈር ጥቃት እንደደረሰባት በመረጋገጡ ጉዳዩን የህግ አካላት እንዲከታተሉት መደረጉን ተናግረዋል።

የህግ አካላት የተፈፀመውን ድርጊት ተከታትለው ሁለቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውለው መዝገባቸውን በህክምና እና በተለያዩ ማስረጃዎች በማጠናከር የምርመራ መዝገባቸውን ለአቃቢ ህግ መላካቸውን ተገልጿል።

አቃቢ ህግም የተላከለትን የምርመራ መዝገብ በመመልከት ክስ የከፈተ ሲሆን ክሱን ሲመለከት የነበረው የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ በዘጠኝ ዓመት እስራት እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ በሰባት ዓመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ለጣቢያች ጨምረው ተናግረዋል።

በምህረት ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *