
በእስር ላይ የምትገኘው የኢራን የመብት ተሟጋች ናርጅስ ሞሃመዲ የ2023 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆና ይፋ ተደረገ።
የ2023 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በዛሬው እለት በኖርዌይ ኦስሎ ይፋ ተደርጓል።ሰላምን በማምጣት እና ስለ ሰላም ለሰሩ ግለሰቦች አሊያም ተቋማት ለሚሰጠው የኖቤል የሰላም ሽልማት ዘንድሮ ከ350 በላይ ግለሰቦች እና ተቋማት በእጩነት ቀርበዋል።
ከእነዚህም መካከል በእስር ላይ የምትገኘው የኢራን የመብት ተሟጋች ናርጅስ ሞሃመዲ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆኗን የኖቤል ኮሚቴ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።የኖቤል ኮሚቴ እንዳስታወቀው ናርጅስ ሞሃመዲ ሽልማቱን ያገኘችው በኢራን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመታገል እና ሰብአዊ መብቶችን እና ነፃነቶችን ለሁሉም ለማዳበር ባደረገችው ጥረት ነው።
በኢራን በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የምትገኘው ናርጅስ መሐመድ የኢራናዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተቋም ምክትል ኃላፊ ነች።
ናርጅስ መሐመድ 13 ጊዜ ታስራ አምስት ጊዜ የተፈረደባት ሲሆን፤ በዚህም በአጠቃላይ 31 ዓመት ጽኑ እስራት እና 154 ጅራፍ ግርፋት ተፈርዶባታል።
በአሁኑ ጊዜ ናርጅስ መሐመድ በተለያዩ ክሶች የ12 ዓመት እስር ተፈርዶባት በቴህራን ኢቪን እስር ቤት ውስጥ እንደምትገኘት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች አስታውቀዋል።የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ የዝንድሮ አሸናፊን የመረጠው 259 ግለሰቦች እና 92 ድርጅቶችን ጨምሮ በድምሩ ከ351 እጩዎች መካከል አወዳድሮ ነው።
የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ 11 ሚሊየን የኖርዌይ ክሮና ወይም 990 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ሽልማት ይበረከትላቸዋል።