መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 25፤2016 – በአዲስአበባ የተከበረዉ የኢሬቻ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት የአዲስአበባዉ የኢሬቻ በዓል የገዳ ስርአቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታዉቋል፡፡

አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የሀገራችንና ከጎረቤት ሀገራት የመጡ እንግዶች እና ቱሪስቶች የታደሙበት የ2016 ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በሰላም እና በልዩ ድምቀት መከበሩን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከግብረ-ኃይሉ ሰምቷል፡፡

ለበዓሉ በሠላም መከበር የድርሻቸውን ለተወጡ ለመላው የኦሮሞ ህዝብ፣ ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና ለመላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ እንዲሁም ለኦሮሞ አባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች፣ ለበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች፣ ለወጣቶችና ለፀጥታ አካላት በሙሉ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት፣ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የመጡ እንግዶችን በገዳ ስርዓት እሴቶች መሰረት በወንድማማችነትና በእህታማማችነት መንፈስ በማስተናገድ ካከናወኑት ተግባር ባሻገር ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው እንዲሁም መላው የፀጥታ አካላት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን በብቃት በመወጣታቸው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንደተከበረ የፀጥታና ደህንነት የጋራ-ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓልም በተመሳሳይ ሁኔታ በሰላም እንዲከበር ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጥሪውን አስተላልፋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *