
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሸካ ዞን የኪ ወረዳ በሠላም በር ቀበሌ በመኖሪያ ግቢያቸዉ ዉስጥ ካናቢስ የተሰኘ አደንዛዥ እፅ ዘርተው ለሽያጭ ሲያቀርቡ የነበሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል ።
ፖሊስ ከህብረተሰቡ በአገኘው ጥቆማ አማካኝነት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በግቢ ዉስጥ የተለያየ መጠን ያላቸዉ የካናቢስ ተክሎች ማግኘቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።
ሁለቱ ግሰቦች በቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራ እየተጣራባቸዉ እንደሚገኝ ተገልጿል ። አደንዛዥ እፅ ወጣቶች የተለያዩ ወንጀሎችን እንዲፈፅሙ የሚገፋፋ ጎጂ ተግባር በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ አክለዋል ።
በቅርቡ በምስራቅ ቦረና ዞን በዋጫሌ ወረዳ ግምታዊ ዋጋው ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ካናቢስ አደንዛዥ እፅ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን መዘገቡ ይታወሳል ።
በተጨማሪም በጂንካ ከተማ ከአሁን ቀደም በግለሰብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ተዘርተው የተገኙ የአደንዛዣ እፅ ተክሎች በፖሊስ እንዲወገዱ መደረጋቸው የሚታወሰ ሲሆን ካናቢስ እና መሰል አደንዛዥ እፆች በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛል ።
በአበረ ስሜነህ